ጆርጅ ማክላሪን እ.ኤ.አ. በ1948 በኦክላሆማ ዩኒቨርሲቲ የገባ የመጀመሪያው ጥቁር ሰው ነው።ይሁን እንጂ ትምህርቱን የተከታተለው በክፍሉ ውስጥ ከነበሩ ነጭ ተማሪዎች ጋር ተቀላቅሎ ሳይሆን የክፍሉ ጥግ ላይ ለብቻው እንዲቀመጥ ተገዶ ነበር። ቢሆንም ስሙ በዩኒቨርሲቲው ምርጥ ሦስት ተማሪዎች አንዱ ሆኖ በክብር ዝርዝሩ ላይ ሰፍሯል።
ስለወቅቱ ሁኔታ ማክላሪን ተጠይቆ ሲመልስ እንዲህ ብሏል፣
”አንዳንድ ተማሪዎች እንደ እንስሳ ነበር የሚያዩኝ፣ አንዳቸውም ሊያናግሩኝ ፍላጎት አልነበራቸውም፣ መምህራኖቹ በክፍሉ ውስጥ ስለመኖሬም ማሰብ አይፈልጉም። ጥያቄዎቼን እምብዛም አይመልሱልኝም ነበር። ራሴን በእውቀት ለማነፅ በግሌ በጣም ብዙ ለፋሁ፣ አነበብኩ፣ በፅናት ተመራመርኩ። በመጨረሻ ልፋቴ ፍሬ ሲያፈራ የክፍሉ ተማሪዎች እኔን መፈለግ ጀመሩ፣ አስተማሪዎቹም ሲያስተምሩ እኔን ግምት ውስጥ ማስገባት ጀመሩ። በሂደት የሁሉም ትኩረት እኔ ላይ እንዲሆን አደረኩ”