የህብረተሰብ ጥናት (Sociology) ማህበራዊ አወቃቀሮችን፣ ስርዓቶችን እና ተቋማትን አመጣጥ፣ እድገት፣ ለውጥ፣ ቀጥተኛ ወይም ስውር ሚና የሚተንተን እንዲሁም የማህበራዊ ንድፈ ሐሳቦችን በሳይንሳዊ መንገድ በመመርመር ማኅበረሰብን ለማሻሻል ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ሃሳቦችን ማበልፀግ ላይ ትኩረት የሚያደርግ አንድ የጥናት ዘርፍ ነው።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን ኦገስት ኮምት (August Comte) እና ካርል ማርክስ (Karl Marx) የህብረተሰብ ጥናት አስፈላጊ የማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል የህብረተሰብን አወቃቀርን እና አሠራርን ለመረዳት የሚጠቅም ዘዴ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ማርክስ የህብረተሰብ ጥናትን ላቅ ያለ ጥቅም ለማስረዳት በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር “ፈላስፋዎች ዓለምን በተለያዩ መንገዶች ተርጉመዋል። ነገር ግን ዋናው ነገር ዓለምን ለሰው ልጆች ተስማሚ ወደ ሆነ ስፍራ መለወጥ መቻል ነው”
በ1972 ሃዋርድ ቤከር (Howard Becker) የተባሉ የተከበሩ የዩናይትድ ስቴትስ የህብረተሰብ ጥናት ንድፈ ሃሳብ ምሁር እንዲህ ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል – “ጥሩ የህብረተሰብ ጥናት … ስለ ማህበራዊ ተቋማት እና ማህበራዊ ክስተቶች ትርጉም ያለው ትንታኔዎችን ያዘጋጃል፣ እንዴት እንደሚፈጠሩ እና እንደሚቀጥሉ ትክክለኛ ማብራሪያዎችን፣ እና የማህበረሰብን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ዝንባሌዎች እንዲሻሻሉ ወይም እንዲወገዱ ጠቃሚ ምክረ ሀሳቦችን ያቀርባል”
አሁን ሀገራችን ላለችበት ማህበራዊ ምስቅልቅል የህብረተሰብ ጥናት (Sociology) እና የዚህ ዘርፍ ባለሙያዎች በሙሉ (Sociologist, Social Workers, Social Anthropologist) አበርክቶ ቁልፍ ሚና ሊኖረው ይገባል።