ከአመታት በፊት ታዋቂዋ አንትሮፖሎጂስት ማርጋሬት ሜድ በአንድ የአንትሮፖሎጂ ተማሪ ይህ ጥያቄ ቀረበላት፤ “የሰው ልጅ ስልጣኔ መነሻ ነው ብለሽ የምታስቢው ነገር ምንድን ነው? ከየትስ ይጀምራል?”
ተማሪው የጠበቀው ማርጋሬት ሜድ ጥንታዊ ስለሆኑ በሸክላ ስለተሰሩ ቁሶች፤ ስለ አደን መሳሪያዎች፤ ስለ ድንጋይ ወፍጮዎች፤ ወይም ደግሞ ሀይማኖታዊ ቅርሶች ትናገራለች ብሎ ነበር።
ነገር ግን የሜድ መልስ ተማሪው እንደጠበቀው አልነበረም!
ሜድ ምን አለች?
“የሰው ልጅ የመጀመሪያ የስልጣኔ ማስርጃ 15 ሺ አመት እድሜ ያለውና አርኪዮሎጂስቶች በቁፋሮ ያገኙት ተሰብሮ የዳነ የሰው የላይኛው የእግር ክፍል አጥንት (ጉልበትን ከሞሃይት ጋር የሚያገናኝው) ነው። ይህ የአጥንት አይነት ከተሰበረ በራሱ ለመዳን ከ6 ሳምንት ያላነሰ ግዜ ይፈልጋል። ዘመናዊ ህክምና በሌላቸው በጥንታዊው ማህበረሰብ ውስጥ ይኖር የነበረ አንድ ሰው ይህ አጥንቱ ተሰብሮ መዳን መቻሉን ይህ በቁፋሮ የተገኝ ቅሪተ-አካል አረጋግጦልናል”
ሜድ ቀጠለች …
“በእንስሳት ሥርወ-መንግስት (animal kingdom) እግርህ ከተሰበረ ተንከባካቢ ስለማይኖርህ የመዳን ዕድል አይኖርህም ፤ ትሞታለህ። ከአደጋ ማምለጥ አትችልም፤ ውሃና ምግብህን ፈልገህ ማግኘት አትችልም።
የእግርህ አጥንት ተሰበረ ማለት በአጭሩ የሌሎች እንስሳት ምግብ ሆንክ ማለት ነው። የትኛውም እግሩን በዚህ ደረጃ የተሰበረ ፍጥረት እግሩ እስኪድን ድረስ በህይወት መቆየት አይችልም። በሌሎች ይበላል አልያም በተደበቀበት ቦታ በርሃብ ይሞታል።
ይሁን እንጂ ይህ ቅሪተ አካል በዚያን ግዜ የነበረ አንድ ሰው የእግሩ አጥንት ተሰብሮ መዳን የቻለ መሆኑን ያሳያል። ይህ የሚነግረን ነገር ይህን ሰው ለማዳን ሌላ ሰው አብሮት ሆኖ ሲንከባከበው እንደነበር ነው! ስብራቱ ድኖ ራሱን እስኪችል ድረስ ቢያንስ ከ6 ሳምንት በላይ ከአጠገቡ አልተለየውም፤ የተሰበረውን ቦታ አስሮለታል ወይም ሸፍኖለታል፤ መግቦታል፤ ከመበላት ተከላክሎለታል፤ ከቦታ ቦታ ተሸክሞ ወስዶታል።
ይህ ተሰብሮ የዳነ የሰው ልጅ ቅሪተ አካል የሚያሳየው ከ15 ሺ አመት በፊት የሰው ልጅ ህይወቱ አደጋ ላይ የወደቀን ወገኑን ለመታደግ ሲያደርግ የነበረውን በጎ ተግባር ነው።፡ ይህ በአስችጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን የመርዳት ባህል ነው ለእኔ የሰው ልጅ ስልጣኔ የመጀመሪያ ምልክት ብዬ የምወስደው”
ሌሎችን ማገልገል እና መርዳት ስልጡንነት ነው፤ ስልጡን እንሁን!